33ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በኢሲሰዩ ተካሄደ
33ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ "ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ መድረክ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ነሀሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ክቡር አቶ ኮራ ጡሽኔ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ባደረጉት ንግግር በከፍተኛ ትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ በተደረገው ጥረት መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ መሆኑንና የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው አያይዘውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባሉባቸው አካባቢዎች የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የሚያሻሽሉ ተግባራትን በማከናወን እንዲሁም በሀገራዊ የልማት መስኮች ተጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባቸውና ከመማር ማስተማርና የማህበረሰብ አቀፍ የምርምር አገልግሎት በተጨማሪ በማህበረሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ በስፋት መስራት እንደሚገባቸው፣ የተቀረጹት የከፍተኛ ትምህርት የሪፎርም አጀንዳዎች ተግባራዊነት ጠንክረው መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ያለውን የሲቪል ሰርቫንቱን አቅም የመገንባት ልዩ ተልዕኮውን ይዞ ከተቋቋመበት ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ለመንግስት ሠራተኞችን አቅም በመገንባት፣ የአመራሩንና የሰው ኃይል እጥረትን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ስራዎችን መስራት የቻለ እና ተልዕኮውንም በብቃት በመወጣት ላይ ያለ ተቋም መሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው ባስመረቃቸው ከ ሰባ ሺህ በላይ ሲቪል ሰርቫንቶች እንዲሁም ባፈራቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚኒስትሮች፣ ከንቲባዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሲመሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንደነበር እና ከዚያም በኋላ ለተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተጠሪ እንደነበር የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ ከ 2014 ጀምሮ ለትምህትርት ሚኒስቴር ተጠሪ እንዲሆን የተደረገ በመሆኑ ትክክለኛ ቦታውን እንዲያገኝ የተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ያለውን የፋይናንስ አሰራር እና የመንግስት ግዥ ሥርዓት መዘመን፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት፣ ለፍትሕና የዳኝነት አገልግሎት መሻሻል፣ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ለማስቻል በከተማ ልማት እና በሌሎችም ተዛማጅ መስኮች ስልጠናዎችን በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም እንዲሁም በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ሀምሳ አራት የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ያለ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 91% የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች መሆናቸውን በመግለጽ በቀጣይም የቅበላ አቅሙን በማሳደግ የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና ጥራት ያለው ትምህርትን ለማህበረሰቡ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል። በመንግስት በጀት ከሚሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ባሻገርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፌዴራል፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ተቋማት እና በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲውች ጋር በመተባበር የተጀመሩ አጋርነቶችን በማጠናከር ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው የምርምርና ማማከር አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በጉባኤው ላይም የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃጸምና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት፣ የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት፣ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት የሪፎርም ስራዎችን ፣ የቁልፍ አፈፃጸም አመላካች ጉዳዮች ላይ ሪፖረቶችና የተለያዩ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የፓናል ውይይትና በቀረቡት ሪፖረቶችና ጽሑፎች ላይም ሰፊ ውይይት ተደረጓል፡፡