G+7 የስልጠና ማዕከል ግንባታ ዉል ስምምነተ ተደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ 687,299,720.41 (ስድስት መቶ ሰማንያ ሰባት ሚሊዮን ሁለት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺ ሰባት መቶ ሃያ ብር) ዘመናዊ የስልጠና ማዕከል የግንባታ ዉል ስምምነት ከ አሴፍ ኢንጅነሪንግ ተቋራጭ ድርጅት ጋር በ 19/4/2016 ዓ.ም አደረገ፡፡ተቋራጭ ድርጅቱ ግንባታዉን በ2 ዓመት ዉስት ገንብቶ ለዩኒቨርስቲዉ እንደሚያስረክብ ገልጿል፡፡
በዉል ስምምነቱ ወቅት የኢሲሰዩ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እንደተናገሩት ይህ ፕሮጀክት በ2 ዓመት የግዜ ገደብ የሚጠናቀቅ ሲሆን በተለይ ዩኒቨርሲቲዉ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ለሚያደርገዉ የሽግግር ሂደት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ ማዕከሉ በዉስጡ የተለያዩ ዘመኑን የዋጁ ማሰልጠኛ ክፍሎች፣ሙዚየሞች እንዲሁም ለአንድ ዘመናዊ ስልጠና ማዕከል የሚያስልጉ ክፍሎች ከተሟሉ ግብአቶች ጋር የሚይዝ ሲሆን ተቋሙን አሁን ካለዉ የስልጠና መዕከል ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረዉ ነዉ ብለዋል፡፡
የፕሮጀክት አሸናፊ አሴፍ ኢንጂነሪንግ ይህን ግንባታ ሲያከናዉን አደራ ጭምር የምንሰጠዉ የፕሮጀክቱ አሸናፊ ድርጅት ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ ሀላፊነቱን በመወጣት ለትዉልድ የሚተላለፍ ግንባታ በመገንባት አሻራዉን ማሳረፍ አለበት ብለዋል፡፡ዩኒቨርስቲዉ የሚገነባዉ ህንጻ ለትዉልድ ተሸጋሪ እንዲሆን ከጅማሪዉ ጀምሮ ትልቅ ትኩረት አድርጎ የሰራ መሆኑን በመግለጽ ይህ ፕሮጀክት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ሂደት በተመለከት የኢሲሰዩ የምህንድስናና ጥገና አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለሙ ሲሳይ እንደገለጹት የስልጠና ማዕከሉ ለመገንባት ግልጽ ጨረታ የወጣ ሲሆን 36 ተወዳዳሪዎች ተወዳድረዉ 6 ተወዳዳሪዎች የተቀመጠዉን መስፈርት ያሟሉ ሲሆን ከእነዚህ ዉስጥም አሴፍ ኢንጅነሪንግ ተቋራጭ ድርጅት በ 687,299,720.41 (ስድስት መቶ ሰማንያ ሰባት ሚሊዮንሁለት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺ ሰባት መቶ ሃያ ብር) እንዳሸነፈ አብራርተዋል፡፡
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አስራት ኤፍሬም እንደገለጹት ከዩኒቨርስቲዉ ጋር ለመስራት እድሉን ስላገኙ ደስተኛ መሆናቸዉን በመግለጽ ማዕከሉን በጥሩ ሁኔታ መርተን በተቀመጠለት የግዜ ገደብ በማጠናቀቅ እናስረክባለን ብለዋል፡፡ አሴፍ ኢንጅነሪንግ ተቋራጭ ድርጅት በ1994 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመስራት ብዙ ልምድ ያለዉ ዉጤታማ ስራ የሰራ መሆኑን ገልጸዉ ይህ ፕሮጀክት በዋናነት የምንሰራዉ ስራ ምስክር እንዲሆን አድርገን እንገነባዋለን ብለዋል፡፡