የኢሲሰዩ ካውንስል የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሚያዚያ 3 ቀን 2015 በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በስብሰባው መክፈቻ ላይ ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ለካውንስሉ አባላት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዩኒቨርሲቲው በለውጥ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው ካውስሉን ለተቀላቀሉት አዳዲስ አባላት የካውንስሉን ኃላፊነትና ተግባራት በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ በዚህም ካውንስሉ ለዩኒቨርሲቲው አመራር የአማካሪነት ሚናን የሚወጣ እንደመሆኑ መጠን የሚቀርበውን ሪፖርት በጥልቀት በመፈተሸ ለቀጣይ አፈጻጸም አቅጫ ለማስቀመጥ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ግብዐት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
የአፈጻጸም ሪፖረቱን ያቀረቡት ዶ/ር አብረሃም ሐጎስ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለ2015 በጀት ዓመት በስምንት ግቦች ከፋፍሎ ያቀደውን ዕቅድ የአፈጻጸም ደረጃ ዝርዝር ለካዉንስሉ አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ሪፖርት መሰረትም ዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ስልጠና አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማሳደግ ባስቀመጠው ግብ መሰረት በ53 የትምህርት ፕሮግራሞች አዲስና ነባር ተማሪዎች እያሰተማረ የሚገኝ ሲሆን በ2015 የትምህርት ዘመን አዲስ ተማሪዎችን በፒኤችዲ ፕሮግራም ለመቀበል በ9 ትምህርት መስኮች (field of specializations) የመግቢያ ፈተና ለመፈተን ካመለከቱ 489 አመልካቾች ለፈተና የተመረጡ 305 ፈተና የወሰዱ ሲሆን ጠንካራ የሆነውን የፈተና ሂደት በማለፍ 60 ተማሪዎችን (58 ወ፣ 2 ሴት) አዲስ የፒኤችዲ ተማሪዎች ቅበላ ተካሂዶ ትምህርት ተጀምሯል፤ 2,248 አመልካቾች ደግሞ በ2016 የትምህርት ዘመን በተከታታይ ትምህርት (ማታ እና ቅዳሜና እሁድ) ተመዝግበው ፈተና ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የተካታታይ ምዘናና የፈተና ጥራት ላይም ክትትልና ድጋፍ የተካሄደ ሲሆን 51 መ/ቤቶች የሠራተኛ ቅጥርና የደረጃ እድገት ፈተና አገልግሎት ጠይቀው ለ41 መ/ቤቶች፣ ለ449 የስራ መደቦችና ለ2000 ተወዳዳሪዎች የፈተና (የምዘና) አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡
ለመጀመሪያ ዲግሪ ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ፣ የቋንቋ ብቃት ስልጠና እና ውጤታቸው ዝቅተኛና ለሆነና ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችን መለየት ቱቶሪያል እንዲሁም ለፒኤችዲ ተማሪዎች ለ6 ቀናት የምርምር ክህሎትን የሚያጎለብቱ በሶስት ዋና ዋና ርዕሶች ላይ አጭር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል 7,000 ኢ-መፅሐፍት ከተለያዩ ድህረ ገፆች በማውረድ ወደ ሲስተም ገብተዉ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ሲሆኑ 26 ኢ-ጆርናሎችን ሰብስክራይብ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ተደርገዋል፤ የመምህር-ተማሪ ጥመርታን ለማሻሻልም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን በዝውውር እና ያለውን አቅም በአግባቡ በመጠቀም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የመምህር-ተማሪ ጥምርታው 1፡11 ማድረስ ተችሏል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ማዕከል (English Language Improvement Center, ELIC) ለማቋቋም የማዕከሉ ቦታ ተለይቶ ማዕከሉን በግብዓት የማደራጀት ስራ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
ለ3084 ሰልጣኞች የብቃት-ተኮር ስልጠናዎችን ተሰጥቷል፤ 9 ሞጅውሎችና 10 አዳዲስ ስልጠናዎች ተቀርፀዋል፤ 5 ሞጁሎች ተከልሰዋል፡፡ ለቀጣይ ክረምትም የሲቪል ሰርቪሱ ወጣት ሰራተኞች ስልጠና ለመስጠት ቡድን ተደራጅቶ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጀምረዋል፡፡
የጥናትና ምርምር፣ የማማከር እና ማህበረሰብ አገልግሎትን ማሳደግ ረገድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተከናወኑት ተግባራትም መካከል በበጀት ዓመቱ 82 ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን 76 የምርምር ንድፈ-ሃሳብ ፁሁፎች ውስጥ በተለያዩ የግምገማ ሂደቶችን የተለዩ 67ቱ የምርምር ንድፎች 7.5 ሚሊዮን ብር የበጀት ድጋፍ ተደርጎላቸው ጥናቶቹ እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ እና በ2015 በጀት ዓመት በምርምር ማዕከላት የሚካሄዱ 10 ጥናቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ከሌሎች ተቋማት ጋርም በውል እየተከናወኑ የሚገኙ በርካታ ማማከርና የምርምር ፕሮጀክቶች መኖራቸው በሪፖረቱ ተጠቅሷል፡፡ የ2013 ዓ.ም እና የ2014 ዓ.ም ዓመታዊ የምርምር ኮንፈረንሶች ፕሮሲዲንግ የአርትዖት እና የዲዛን ሥራዎች ተጠናቅቀው በሕትመት ሒደት ላይ ይገኛሉ፡ 42 በ2014 የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎች በዩኒቨርሲቲው ጆርናሎች እንዲታተሙ የምርምር ፁኁፎች ለሚመለከታቸው ጆርናሎች ገቢ ተደርገው የአስተችቶ (review) ስራ ተካሂዷል፡፡ በ2014 የተከናወኑ እና 19 በሙስና እና ድለላ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች በውስጥ አስተችቶት ሒደት አልፈው በባለ ድርሻ አካላት ቀርበው ግብዓት ተገኝቶ የመጨረሻዎቹ የምርምር ሪፖርቶች በሕትመት ዝግጅት ሒደት ላይ ሲሆኑ የተለያዩ ሴሚናሮችም ተካሂደዋል፤ ለ2015 ዓ.ም 8ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ለማካሄድ የዝግጅት ስራዎች እየተካሄዱ ሲሆን የ4 ጆርናሎች ሕትመትና ስርጭት ስራ ተካሂዷል፤
የማህበረሰብ አገልግሎትን ከማሳደግ ረገድ 25 ሼዶች ግንባታ በመጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ የዝግጅት ስራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች በቡድን በማደራጀት እና የንግድ ስራ ንድፍ በማዘጋጀት ዩኒቨርሲቲው ካስገነባቸው ሼዶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በዩኒቨርቲው አዲሱ መዋቅር መሰረት በአካዳሚክ ዘርፉ ስር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬትን የሚመራ የሰው ኃይል ተመድቧል፤ በሁሉም ኮሌጆችና በስልጠና ማዕከል በት/ክፍል ደረጃ ተደራጅቶ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ በትምህርት ክፍል ደረጃም የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን፣ ምዘና እና አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን የሚቆጣጠር እና የሚያረጋግጥ ሶስት ሶስት አባላት ያሉት ቡድን ተቋቁሟል፡፡ የድህረ-ምረቃ የመመረቂያ የምርምር ጽሁፍ አዘገጃጃት መመሪያ እና የድህረ ምረቃ የምርምር ፖሊሲ ሰነድ በሴኔት ተገምግሞ፣የማሻሻያ ሀሳቦች ተሰጠውበት እና ፀድቆ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሌጅስሌሽን ለመከለስ ቡድን ተደራጅቷል፤
በዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይልና ተቋማዊ አቅምና ብቃት ለማጎልበት በተቀመጠው ግብ ለማሳካት በተደረገው ጥረትም ዩኒቨርሲቲው ያስገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለዩኒቨርሲቲው ለ153 የአካዳሚ ሰራተኞችና የአስተዳደር አመራሮች የመኖሪያ ቤታቸውን በእጣ ድልድል እንዲያውቁ የተደረገ ሲሆን ሰራተኞች በቅርቡ በመኖሪያ ቤቶች መኖር ይጀምራሉ፤
አዲሱ የዩኒቨርሲቲው መዋቅር ትግበራ እየተካሄደ ሲሆን በአካዳሚ ጉዳዮች ዘርፍ እና በምርምርና ትብብር ዘርፍ ባሉ የአመራርነት መደቦች ላይ በውድድር የአመራር ምደባ ተካሂዷል፤ በአስተዳደርና ልማት ዘርፍ እና በፕ/ጽ/ቤት ስራ ባሉ የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ የአመራርና ባለሙያ መደቦች ላይ ምደባ ለማካሄድም ውድድር እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም 57 ፒኤችዲ ያላቸው መምህራን ቅጥር ለማካሄድ ማስታወቂያ በማውጣት መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ 37 መምህራን ቅጥር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲውም ከረዳት ፕሮፌሰር እስከ ሙሉ ፕሮፌሰር የአካዳሚክ ማዕረግ ያላቸውን መምህራን 52.83 % ለማድረስ ተችሏል፡፡ እስከአሁ በነበሩት አራት ዙሮች 123 መምህራንን በከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም (HDP) በዩኒቨርሲቲያችን በማሰልጠን ለማስመረቅ የተቻለ ሲሆን በ2015 የትምህርት ዘመን 23 መምህራንን በከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም (HDP) እየሰለጠኑ ይገኛል፡፡
አሰራሮችን ቴክኖሎጂ የተደገፉ ከማድረግና መሰረተ ልማቶችን ከማዘመን አካያም በረካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን አሰራሮችን በአውቶሜሽን እንዲደገፉ የማድረግ ፣ IFMIS፣ICMIS፣SIMS አሰራሮችን የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እዲቀጥል ሲደረግ HEIMS (Higher Education Information Management System) በዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል፤ በe-learning ሊሰጡ የሚችሉትን ኮርሶችና የትምህርት ክፍሎች መለየት፣ በተለየው ፍላጎት መስረት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፤ የ 5 ጆርናል ዌብሳይቶች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለምተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር የፕላጃሪዝም መተግበሪያ (Plagiarism Software) ግዥ ተካሂዶ፣ በትምህርት ክፍሎችና በምርምር አበልፅጎት ማዕከል በሚገኙ ኮምፒውተሮች በመጫን ተደራሽ ተደርጓል፤ ተጨማሪ የፕላጃሪዝም ሶፍትዌር ተደራሽ ለማድረግ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
አጋርነት፣ ትስስር እና አለማቀፋዊነትን ማሳደግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በረካታ ስራዎች መሰራታቸውና ከተለያዩ ከሀገር ውስጥና በውጪ ከሚገኙ ተቋማት ጋር አጋርነትና ትብብር ተፈጥሯል፡፡
የበጀት፣ የፋይናንስ፣ የንብረት አስተዳዳር አገልግሎትን ውጤታማነትን ማሻሻልና የውስጥ ገቢ ከማሳደግ አኳያም ከትምህርት ከስልጠና፣ ከመስተንግዶ፣ ከማማከር አገልግሎት ክፍያ አስከ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ያልተጣራ የውስጥ ገቢ ድምር ብር 42,448,399.89 ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለ 2015 ዓ.ም ከተመደበለት ጠቅላላ በጀት ብር 516,114,832.00 ውስጥም አጠቃላይ ወጪ ቅድመ ክፍያን ጨምሮ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም 356,753,391.73 (70.36%) የተጠቀመ ሲሆን የክፍያ ሰርትፊኬት የቀረበለት(ካፒታል በጀት) ብር 80,960,577.40 ሲወራረድ አጠቃላይ የዘጠኝ ወራት የበጀት አፈጻጸሙ 86.24 % የሚደረስ መሆኑና ይህም ጥሩ የሚባል አፈጻጸም ላይ የሚገኝ መሆኑ በሪፖርቱ ቀረቧል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ አገልግሎት እንዲሰጡ ካስገነባቸው ግንባታዎች መካከል ግንባታቸው የተጠናቀቁት የፕሬዚዳንት ህንፃን ጨምሮ ጊዜያዊ ርክክብ በማድረግ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ሲደረግ ሌሎችም በዋናው ግቢ የተካሄዱ ግንባታዎችን ጊዜያዊ ርክክብ ለማካሄድ በመጠናቀቅ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ከሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል የማጠናቀቂያ ፈተና ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች ማከናወኑ በሪፖረቱ ላይ የቀረበ ሲሆን አሁንም በትምህርት ሚኒስቴር ለተመለመሉ እና ሀገር አቀፍ የመጀመሪያ ድግሪ መውጫ ፈተና ለሚያዘጋጁ ምሁራን የምግብ፣ የመኝታ፣ የኮምፒውተር ላብራቶሪዎች እና መሰል አገልግሎቶች በመስጠት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመስራት ላይ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በቀረበው ዝርዝር ሪፖርት ላይም የካውንስሉ አባላት የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት አሳብና አስታየቶችም ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በግምገማው ማጠቃለያ ላይም ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በሰጡት ማጠቃላያ በካውንስሉ አባላት በስፋት በተነሳው አስተያየት እና ጥያቄ መካከልም ለመማር ማስተማር ተግባሩ የሚያስፈልጉ ግብዐቶች በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት ለማሟላት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው EGP ስርዓት ጋር የተያያዙ እና ሌሎች ሀገራዊ ምክንያቶች የመጓተት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው በተቻለ አቀም ሁሉ ግብዐቶችን የማሟላት ስራ ግን እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ የተማሪዎች ቅበላም በትምህርት ክፍሎች ሳይሆን ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ቅበላ በኩል እንዲሆን መደረጉን አስመልክቶም የትምህርት ክፍሎች ያሉበትን ቁመና የመገምገምና የውስጥ አሰራርን የማጠናከር አስፈላጊነትን ጠቅሰው ተቋሙን ለአደጋ እንዳይጋለጥ በማእከል፣ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን በዚህም ያለእንከን በዉጤታማት እየተተገበረ መሆኑን ለካውንስሉ አብራርተዋል፡፡ የትምህርት ክፍሎችም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመመካከር አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን የመክፈትና ነባሮችንም የመከለስ ስራ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡