የኢሲሰዩ ካውንስል በኢሲሰዩ የ5 ዓመታት የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ውይይት አደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል በዩኒቨርሲቲው የአምስት ዓመታት (2016-2020 ዓ.ም) የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ሚያዚያ 3 ቀን 2015ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡ የሪፎርም አጀንዳው የተዘጋጀውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ የተለየ የትኩረት መስክ የያዘ በመሆኑ አዳዲስ የአሰራርና የሪፎርም ስራዎች አስፈላጊ በመሆናቸው የተዘጋጀ ሲሆን ውይይት የተደረገበት ዓማላም ዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃና ምርምር ዩኒቨርሲቲ በመሆኑና አዲስ መዋቅር ተግባራዊ ማድረግ ከመጀመሩ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የአደረጃጀት፣ የስራ ስምሪት፣ እና የለውጥ አጀንዳዎች ላይ ግንዛቤ በመፍጠርና በማሻሻል ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ የሪፎርም አጀንዳዎቹን ለካውንስሉ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን የተዘጋጀው ሪፎርም ከትምህርት ሚኒስቴር የድህረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ስታንዳርዶች፣ ራስ-ገዝ ዩነቨርሲቲ መሆን፣የትምህርት ጥራትና አግባብነት ማሳደግ፣የምርምር ምርታማነትና ተፅዕኖ ማሳደግ፣ የማህበረሰብና ሙያዊ አገልግሎት አፈፃፀም ማሳደግ፣ትብብር፣ትስስርና አለማቀፋዊነትን ማሳደግ፣ የሰው ሀይል ልማት፣ስምሪት፣ ክትትልና ድጋፍ እና የአፈፃፀም ምዘናና ማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድህረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ስታንዳርዶችና የኢሲሰዩ አፈፃፀም አስመልክቶም በትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠው መለኪያ መሰረት ዩኒቨርሲቲው ባለው የአካዳሚክ ሰራተኛ የሰው ኃይል ስብጥር፣ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ቅበላ፣የምርምር በጀት ድርሻ ጥሩ በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነና በሌሎቹ ማለትም በሀገር ውስጥ ካሉ ተቋማትና ኢንዱስተሪዎች ጋር በትብብር የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ባሉት መለኪያዎችም በመካከለኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቀዳሚነት በተቀመጠው የሪፎርም አጀንዳ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመሆን ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲው የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት እቅድ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚተገብርና ለመንግስት ተጠሪ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን ከመንግስት በተወሰነ ደረጃ በጀት ማግኘቱን ይቀጥላል፤ በሂደትም ከራሱ ገቢ፣ ከረጂ እና አጋር አካላት የበጀት ድጋፍ በማሰባሰብ ከመንግሰት የበጀት ጥገኝነት ቀስ በቀስ የሚወጣ ይሆናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው አሁን ያለውን ተልዕኮ፣ እሴቶችና ስትራቴጂያዊ ግቦችን ይዞ በመቀጠል በቀጣይም የግል ተቋማትና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ያማካለ እንቅስቃሴ የሚያካሂድና ነፃ በሆነ አግባብ አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ነፃነቱን ጠብቆ የሚሰራ ተቋም እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የመሆን አላማውን ለማሳካትም በተቋም ደረጃ ዝርዝር እቅድ ማውጣት፣ ተግባራዊ ማድረግ፣ ክትትልና ድጋፍ ማድረግን አስፈላጊነት እና ዘላቂና አስተማማኝ የውስጥ ገቢን ማልማትና ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ላይ ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበትም ፕ/ር ፍቅሬ ለካውንስሉ ገልጸዋል፡፡
ከሁለተኛው የሪፎርም አጀንዳ ማለትም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ከማሳደግ ጋር ተያይዞም በሪፎረሙ ጥራትና አግባብነት ያላቸው የትምህርት ፕሮግራሞችን መቅረፅ፤ ነባር ፕሮግራሞችን መከለስና መሻሻል፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ማድረግ፣የባለ ድርሻ አካላትን ማሳተፍ፤ሀጋራዊ ፋይዳ ያላቸው፣ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ አዳዲስ ድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን መቅረፅና ተግባራዊ ማድረግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ የትምህርት ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ተግባራዊ ማድረግ፣የመምህራንን የማስተማር ክህሎት በስልጠና ማሳደግ እና ሌሎችም በርካታ አጀንዳዎች የተካተቱ ሲሆን በመማር ማስተማር ጥራትን የሚያስጠብቁ አሰራሮችን፣ስታንዳርዶችን በጥብቅ ዲስፕሊን መፈፀም እንደሚያስፈልግም በሪፎረሙ ላይ ተካቷል፡፡
የምርምር ምርታማነትን እና ተፅዕኖ ማሳደግን በተመለከተም የምርምር የበጀት ድጋፍ ማሳደግና ከረጂ እና አለማቀፍ ተቋማት የሚገኝ የምርምር ድጋፍ በማሳደግ የበጀት ድጋፍ ምንጭን ማስፋት፤ ምርምሮች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ማስቻል፤ ምርምርን በጭብጠ ሰፊ ማደራጀት፣ የምርምር ሀብትን በተመረጡና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ሁኔታ መደልደል፤ የምርምር አመራርና አስተዳደር ስርዓት ማጠናከር፤ የድህረ ምረቃ ምርምሮችን ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል፤ ለአካዳሚክ ሰራተኞችና ተማሪዎች በምርምር ስራዎች፣ኮንፈረንሶች እና ዎርክሾፖች አንዲሳተፉ ማበረታታት በሪፎርሙ የተካተቱ ዓበይት ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህን የሪፎርም አጀንዳዎች በተግባር ለመተርጎምም በዩኒቨርሲቲው ባሉት የትምህርት ክፍሎች 3-5 አባላት የምርምር ቡድንኖች እንደሚደራጁና እነዚህም የምርምር ቡድኖች ልምድ ያላቸውን መምህራን ከወጣት መምህራን ጋር በማቀናጀት እና የምርምር ስራ የሚያስፈልገውን ተመጋጋቢ የሙያ እና ክህሎት ስብጥር ያላቸውን አባላት የያዘ ሆኖ የሚደራጁ መሆኑን ፕ/ር ፍቅሬ ገለጸው፤ ማንኛውም አካዳሚክ ሰራተኛ በዚህ የምርምር ቡድን ውስጥ የመሳተፍ ግዴታ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ የምርምር ቡድኖች ዩኒቨርሲቲው በሚፈጥረው የምርምር ስራዎች በውድድር በመሳተፍ ጭብጠ ሰፊ የምርምር ስራዎች ላይ የሚሳተፉም ይሆናል፡፡
የምርምር በጀት ድልድልን በተመለከተም የምርምር በጀት ከ2016 ጀምሮ በቋሚነት ለ3 ኮሌጆች ፣ ለአንድ ስልጠና ኢንስቲትዩት እና ለህግ ትምህርት ቤት የምርምር ቡድኖችን ብዛትን መሰረት አድርጎ ድልድል ይካሄዳል፡፡ ይህ በጀት ለጭብጠ ሰፊ (thematic research) የምርምር ስራዎች የሚውል ሲሆን በኮሌጆች እና ትምህርትክፍሎች በተደራጁ የምርምር ቡድኖች አማካኝነት ውድድርን መሰረት አድርጎ ጥቅም ላይ የሚውል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ለምርምርና ማማከር ማዕከላት በጀት የሚመደብ ሲሆን በተጨማሪም ከሌሎች አካለት በሚያገኙት የምርምርና ማማከር ፕሮጀክቶች ገንዘብ ድጋፍ በማዕከላቱ በተለዩ thematic area ላይ ለሚካሄድ ምርምር ጥቅም ላይ ይውላል፤ ማዕከላቱ በዩኒቨርሲቲው ያሉ የምርምር አደረጃጀቶችን በማወዳደር ምርምር የሚያሰሩ እንደሚሆኑ፤ ለአካዳሚከ ሰራተኞች የምርምር በጀት ድጋፍ በተመለከተም በዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አማካኝነት ለአካዳሚክ ሰራተኞች ውድድርን መሰረት ያደረገ የምርምር በጀት ድጋፍ እንደሚደረግ የምርምር ስራዎችን ሂደት፣ አፈፃፀም፣ ክትትልና ምዘና አንዲሁም ሊከተሉትየሚገባውን አሰራሮችና ስታንዳርዶች የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ዘርፍ በበላይነት እንደሚመራውና እንደሚያስተባብረውም ፕ/ር ፍቅሬ ለካውንስሉ አስገንዝበዋል፡፡
በሌላኛውና የማህበረሰብና ሙያዊ አገልግሎት አፈፃፀም ማሳደግን ጋር ተያይዞ በቀረበው የሪፎርም አጀንዳ መሰረትም የምርምር ስራዎችን ለሌሎች ተቋማት መገምገም፣ መፈተን፤ የካሪኩለም ክለሳ ማካሄድ የመፅሐፍ ግምገማ ማካሄድ፤ የምርምር ስራዎችን በሰሚናሮች፣ ዎርክሾፖች እና ኮንፈረንሶች ማቅረብ፤ ለተማሪዎች ነፃ የቱቶሪያል ትምህርት መስጠት፤ በተለያዩ ሚዲያዎች ሙያዊ ገለፃ ማካሄድ፤ ለተለያዩ መንግስታዊ እና ነፃ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለሚሰጡ ተቋማት ያለክፍያ የሙያዊ አገልግሎቶችን መስጠት እና በማህበረሰብ ስራዎች ነፃ የፈቃደኛ አገልግሎት መስጠት፣ መሳተፍን የመሳሰሉ አበይት ጉዳዮች የሪፎርሙ አካላት ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም እነዚህን ዐላማዎች ለማሳካት በትጋት መንቀሳቀስ እንደሚገባው ተልጸዋል፡፡
ትብብርና ትስስርና ማሳደግን በተመለከተም ዩኒቨርሲቲው የመሰረታቸው ትስስሮች አሁን ያሉበት ደረጃ ሲታይ በሀገር ውስጥ ተቋማት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ እና ከውጭ ሀገር ከሚገኙ መሰልና ረጂ ድርጅቶች ጋራ የዩኒቨርሲቲውን የትምህርትና የምርምር ስራ በገንዘብ እና በቴክኒክ ድጋፍ ሊያግዙ ለሚችሉ የአለማቀፍ እና ረጂ ድርጅቶች በስፋት ማስተዋወቅ፤ ውጭ ሀገር ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን በጋራ የትምህርት ፕሮግራሞችን መስጠት፤ ዩኒቨርሲቲው በዕቅድ ታግዞ ውጤታማ ትብብሮችን እና ትስስሮችን በመፍጠርና በማልማት የበጀት ምንጭ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ በሪፎርም አጀንዳው ላይ ተቀምጧል፡፡
የሰው ሀይል ልማት፣ስምሪት፣ ክትትልና ድጋፍ፤ የአፈፃፀም ምዘና ማሻሻልን አስመልክቶም ኮሌጆች የት/ሚኒስቴርን የድህረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲን ዝቅተኛ የአካዳሚክ የሰው ኃይል ስታንዳርድን ማሟላትና የ60-25-15 የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ስምሪት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በ2016 ዓ.ም ሁሉም የአካዳሚክ ሰራተኛ አዲስ የተሻሻለ የስራ ውል የሚገባ መሆኑ በሪፎርም አጀንዳው ላይ የተቀመጠ መሆኑንና የአካዳሚክ ሰራተኞች የስራ አፈፃፀም ምዘናም 60% ማስተማር፣ 25% ምርምር እና 15% ማህበረሰብና ሙያዊ አገልግሎት እንደሚሆን ፕ/ር ፍቅሬ በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡
የምርምር ስራዎች አፈፃፀም ምዘና በተመለከተም አንድ የአካዳሚክ ሰራተኛ በሴሜስቴር ቢያንስ በአንድ የምርምር ስራ ላይ ሲሳተፍ ለምርምር ስራዎች ከተሰጠው 25% አንፃር ውጤት የሚሞላለት መሆኑንና ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ ለምርምር ስራዎች በጀት ያላገኘ የአካዳሚክ ሰራተኛ ከሚሰራበት የትምህርት ክፍል ጋር በመነጋገር Literature based የሆኑ የምርምር ስራዎች ማለትም Meta-Analysis የመሳሰሉ የምርምር ስራዎችን በሴሜስቴር 1 የምርምር ፅሁፍ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበት፤ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች አፈፃፀም ምዘና ጋር ተያይዞም አንድ የአካዳሚክ ሰራተኛ በሴሜስቴር ቢያንስ በአንድ የሙያ ወይም የማህበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ ከ15% ለማህበረሰብ አገልግሎት አፈፃፀም ምዘና የሚሞላለት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላትም በሪፎርሙ ላይ በተካተቱት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሀሳብና አሰተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ለተነሱት ሀሳብና አሰተያየቶችም ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ተጨማሪ ገለጻና ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ በማጠቃለያም የዩኒቨርሲቲው ካውንስል ስለ ሪፎርሙ በቂ ግንዛቤን በመያዝ ከወዲሁ ግብዐቶችን ማሰባሰብ እና በቀሩት ሶስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መስራት እና ማጠናቀቅ፤ በተጨማሪም በሀገርአቀፍደረጃ የተቀረጹ የሪፎርም ስራዎች ለዩኒቨርሲቲዉ በተሰጠዉ የትኩረት መስክ ጋር በማስተሳሰር መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡