2016 የበጀት ዓመት የላቀ ዉጤት ላመጡ የስራ ክፍሎች ሽልማት ተሰጠ
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በ2016 የበጀት አመት የላቀ ዉጤት ላመጡ የስራ ክፍሎች የእዉቅና እና ሽልማት ፕሮግራም ተደረገ፡፡ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደዉ ዓመታዊ የሰራተኞች ቀን ላይ በበጀት አመቱ በስራቸዉ ያሉ ሰራተኞችን በመምራት እና ጥሩ የስራ መንፈስ በመፍጠር ዉጤታማ የሆኑ ሶስት የስራ ክፍሎች የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተበረከተላቸዉ፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ይህ ሽልማት ባለፉት ግዚያት የተቋረጠ ቢሆንም በዘንድሮ በጀት ዓመት ማናጅመንቱ በወሰነዉ ዉሳኔ እና ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ተጀምሯል ብለዋል፡፡ሁሌም እንደመርህ የምንለዉ ዩኒቨርስቲያችን ሲያድግና ሲለወጥ የመንግስት ተቋማትና ሰራተኞች የተሻለና ጥራት ያለዉን አገልግሎት ያገኛሉ፤ በተጨማሪም ሰራተኞች ያድጋሉ፣ይለወጣሉ በሰሩት ልክ ተጠቃሚም ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የዚህ የእዉቅና እና ሽልማት ዋንኛ ዓላማ በሰራተኞች እና ስራ ክፍሎች መካከል የዉድድር መንፈስ በመፍጠር ለተሻለ ስራ እንዲተጉ ማድረግ ሲሆን በተጨማሪም በዚህ ሂደት ዉጤታማ ለሆኑ ክፍሎች እዉቅና እና ማበረታቻ መስጠት ነዉ ብለዋል፡፡በዘንድሮ አመት ሶስት የስራ ክፍሎች ለአፈጻጸማቸዉ እዉቅና የተሰጠ ሲሆን በሚቀጥለዉ በጀት ዓመት ደገሞ ቁጥሩን በመጨመር በሌሎች ዘረፎች ጭምር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ለሲቪል ሰርቪሱ የምንሰጠዉ አገልግሎት መሻሻል እንደተጠበቀ ሆኖ የዩኒቨርስቲያችንን የዉስጥ አቅም በብቁ እና በቂ የሰዉ ኃይል በማሳደጋችን ፣ ለመማር ማስተማሩ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማት በማስፋፋታችን፤ ሌሎች መስፈርቶች ጭምር በማሟላታችን የምርምር ዩኒቨርስቲ መዋቅር ማግኘት ችለናል ብለዋል፡፡ አሁንም ከዚህ በበለጠ ዩኒቨርስቲያችንን ለማሳደግ በተሰማራንበት የስራ ክፍልና የስራ ድርሻ በተነሳሽነት መንፈስ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡በመጨረሻም ለዩኒቨርስቲዉ ዕቅድ ክንዉን መሳካት የበኩላቸዉን ኃላፊነት ለተወጡ አመራሮች፣የአካዳሚክና የአስተዳደር ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በማጠቃላያዉም ላይ በ2016 ዓ.ም በአስተዳደር እና ልማት ዘርፍ የፋይናንስ ሥራ አስፈጻሚ፣የምህንድስና እና ጥገና አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ እና የስልጠናና ፋሲሊቲእና መስተንግዶ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ በክፍል ደረጃ የእዉቅና እና የዋንጫ ሽልማት ፣ ለስራ አስፈጻሚዎቹ የአስር ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡