በኢሲሰዩ በቁልፍ ተግባር አመላካቾች አፈጻጸም ላይ ስልጠና ተሰጠ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (የኢሲሰዩ) ከኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመው በቁልፍ ተግባር አመላካቾች አፈጻጸም መሰረት፣ ለ130 የአካዳሚክ አመራሮች በቁልፍ የውጤት አመላካቾች የአተገባበር ስልቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የሁለት ቀን ስልጠና ተሰጠ፡፡
የካቲት 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ/ም የተሰጠው ስልጠና ያዘጋጁት በዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት እና የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት በመተባበር ሲሆን፣ ስልጠናው የተሰጠው ከትምህርት እና ስልጠና ጥራት ባለስልጣን በመጡ ከፍተኛ ኤክስፐርቶች መሆኑ ታውቋል፡፡ ስልጠናው ያተኮረባቸው ነጥቦችም በከፍተኛ ትምህርት የጥራት ማረጋገጫ አጠቃላይ እይታ፣ የእውቅና ሂደት እና ስነስርዓቶች (Accreditation Process and Procedures)፣ የእውቅና ደረጃዎች (Accreditation Standards)፣ የዳታ ማሰብሰቢያ መሣሪያ እና መመሪያው፣ የተማሪ እርካታ ዳሰሳ ፣ የጥራት ኦዲት እና በውጤት ላይ የተመሰረተ ትምህርት ፕሮግራም (Outcome-Based Education) እና ስርዓተ ትምህርትን በማዘመን የትምህርት ጥራትን ማሳደግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ስልጠናውን አስመልክተው የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተመስገን ቢረጋ እንደተናገሩት፣ ስልጠናው በየደረጃው ላሉ የዩኒቨርሲቲው የትምህርት አመራር ኃላፊዎች ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በሰኔ ወር ዩኒቨርስቲዉ አክሪዲቴሽን ለማሰጠት ላቀድቸው ዘጠኝ ፕሮግራሞች ስኬት ቁልፍ ሚና ያለው እና የአተገባበር ብዥታንም ለማጥራት የሚረዳ ስልጠና እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርስቲዉ እየተተገበረ ያለዉ የቁልፍ ተግባር አመላካቾች ትግበራ ቀደም ሲል ተከታታይነት ያለው ውይይት እንደተካሄደበት እና በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርም የተሰጠውን አቅጣጫ አስታውሰው፣ “ይህ ትግበራ በተቀመጠለት አመላካቾች ተመዝኖ ተቀባይነትን ማግኘት አለበት’’ ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ተሳታፊዎች እስከ ሰኔ 2017 ዓ/ም ድረስ ለሚፈጽሙት ተግባር አክሽን ፕላን እንደተዘጋጀ አብራርተዋል፡፡