የኢሲሰዩ ፕሬዚዳንት ከአካዳሚክ እና ምርምር ዘርፍ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ ከአካዳሚክ እና ምርምር ዘርፍ ካሉ አመራሮች ጋር በ 24/6/2017 በሴኔት አዳራሽ የትውውቅና የውይይት መድረክ አካሄዱ፡፡
በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ወደፊት በጋራ ዉጤታማ ስራ ለመስራት ትዉዉቅ አስፈላጊ መሆኑን፣ በዩንቨርስቲዉ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች ትዉዉቁ እንደሚቀጥል ገልጸዉ ተቋሙ ያሉትን ጥሩ ተሞክሮች ማስቀጠል እና አዳዲስ አሰራሮች መተግበር፤ በተጨማሪም ይህ ተቋም አሁን አለም በደረሰበት ደረጃ ማድረስ እና ዘመኑ የሚፈልገዉን አሰራር በተቋሙ መተግበር ግድ የሚል መሆኑን በመጥቀስ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ያለዉ የሰዉ ሀይል እንደተቋም እንደሀገርም ትልቅ ሀብት ስለሆነ ያሉትን አቅም ተጠቅመን እንደ ተቋም የተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመገንዘብና ያሉ ሀብቶችን እንዲሁም ዕድሎችን በመጠቀም በትጋት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ተቋሙን በሁሉም መስኮች በሀገርና በአህጉር ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግም አዲሱ አመራር መዘጋጀቱን የገለጹት ፕሬዝንዳቱ ይህንን ራዕይ በመገንዘብ በዩኒቨርሲቲው ለምርምር ከሚበጀተው በጀት ባሻገር ሀገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮችን በመፍጠር ተጨማሪ የምርምር ፈንዶችን ለማግኘት ትልቅ ትኩረት በመስጠት በእቅድ መሥራት እንደሚጠበቅ አጽንኦት ሰጥተዉ አሳስበዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ ም/ፕሬዘንዳት የሆኑት ዶ/ር ለማ ጉዲሳ፣ በዘርፉ ያለውን የስራ አፈጻጸም በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ በመማር ማስተማር ሂደት ያሉትን አሁናዊ መረጃዎች፣ ዋናዋና ተግዳሮቶች፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን እና አስቸኳይ ስራዎችን አካተው አቅርበዋል፡፡በማስከተልም በዶ/ር አለማየሁ ደበበ የምርምርና ትብብር ዘርፍ ም/ፕሬዚዳንት በየዘርፋቸዉ የተከናወኑ አንኳር አንኳር ስራዎች እና በየዘርፉቸዉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም ተሳታፊ የአካዳሚክ አመራሮቹ ተጨማሪ አስተያየቶችን እና ለተግዳሮቶቹ መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን ሃሳቦች አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም በየዘርፉ ያሉ አመራሮች ላቀረቡአቸዉ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ፕሬዚዳንቱ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ትኩረት የሚሹ ስራዎች ቅድሚያ እንደሚሰጡ ገልጸዉ ፣የተነሱ ሀሳቦች በመውሰድ እንደተቋም በሚለዩ ስትራቴጂክ የትኩረት አቅጣጫዎች እና የሪፎርም ስራዎች ላይ ለዩኒቨርስዉ ማህበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር እና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ትግበራ መግባት ዋናዉ የውይይቱ እና ትዉዉቁ ዓላማ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡