ኢሲሰዩ በአካባቢው ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ስልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (የኢሲሰዩ) በምርምርና ማማከር ዘርፍ የማህበረሰብ ተሳትፎን፣ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን እና ቴክኖሎጂን ሽግግር ዳይሬክቶሬት፣ በዘርፉ ለ2017 ዓ.ም በተያዘው አጀንዳ መሰረት፣ በአካባቢው በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ መምህራንና የትምህርት አመራር ባለሙያዎች የሁለት ቀን ስልጠና ሰጠ፡፡
መጋቢት 6 እና 7 ቀን 2017 ዓ/ም የተሰጠው ስልጠና የተዘጋጀው በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አሳታፊነትና ኢንዱስተሪ ትስስር ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በኩል ሲሆን፣ በስልጠናው፣ ማስተማር እና ምዘና ዘዴዎች (Instructional and assessment methods)፣ የትምህርት አመራር እና አስተዳደር (Educational leadership and management) እና ቱቶሪያል ፕሮግራሞች (Tutorial programs) የሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ተካተውበታል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት በዩኒቨርሲቲው በማስተማር ስነ ዘዴ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ስልጠናውን አስመልክተው ማህበረሰብ አሳታፊነት፣ ኢንዱስተሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዮናስ አበሻ እንደተናገሩት፣ በዩኒቨርሲቲያችን እንዲህ ያለው ስልጠና ሲሰጥ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይነት ያለው ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ከተሳተፉ የትምህርት ባለሙያዎችን ከስልጠናው ምን እንዳተረፉ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ በስራው ላይ ብዙ ከመቆየት ከሚመጣ ዘልማዳዊ አሰራር ተላቆ ወደ ሳይንሳዊ የማስተማር ዘዴ የሚመልስ ስልጠና መሆኑን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው እንዲህ ያለውን ስልጠና አጠናክሮ ቢቀጥል እና ስልጠናው ለሁሉም መምህራን ቢዳረስ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡