የኢሲሰዩ በአካባቢው ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ/ም በአካባቢው ከሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 44 በጎ ፍቃደኛ ተማሪዎች በመንገድ ደህንነት እና በትራፊክ አደጋ አስከፊነት ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡
ተማሪዎቹ የተውጣጡት ከሮፋም አካዳሚ፣ ከሳፋሪ አካዳሚ፣ ከሂልሳይድ ሁለተኛ ደረጃ እና ከጊብሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ ስልጠናን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማማከር ዘርፍ ማህበረሰብ አሳታፊነትና ኢንዱስተሪ ትስስር ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ነው፡፡
በስልጠናው የትራፊክ አደጋ መንስኤ ተጽዕኖ እና የመከላከያ ዘዴዎች፣ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች፣ የትራፊክ አደጋ ዋና ዋና ምክንያቶች፣የትራፊክ አደጋ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ አምስቱ ስልቶች በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱበት መሆኑን ከስልጠናው ምርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት አቶ ዮሐንስ ለማ ከፌደራል ትራፊክ ማኔጅመንት፣ ዶ/ር በለጠ እጅጉ ከኢሲሰዩ ከተማ ልማት ኮሌጅ እና አቶ መንግስቱ አድማሱ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን መሆናቸውን የማህበረሰብ አሳታፊነት፣ ኢንዱስተሪ ትስስር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አበሻ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ዮናስ አስከትለውም ስልጠናው ዩኒቨርሲቲያችን በዘርፉ ለ2017 ዓ.ም በተያዘው እቅድ መሰረት፣ በአካባቢው ከሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይነት ያለው ስልጠና ለመስጠት ባቀደው መሰረት እየተከናወነ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞቹም በዛሬው ዕለት ማለትም መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ከበጎ ፈቃድ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ጋር በመሆን ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በንድፈ ሀሳብ የወሰዱትን ስልጠና ወደ ተግባር በመለወጥ፣ ከሂል ሳይድ ትምህርት ቤት ወደ ኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሚወስደው መንገድ ላይ የትራፊክ ማስተናበር መርሃግብርን አካሂደዋል፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ከየካ ክፍለከተማ ፖሊስ መመሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ማስተባበሪያ የመጡ የትራፊክ ቁጥጥር ፖሊስ ኃላፊዎች እና አባሎች ተገኝተው ግንዛቤ አስጨብጠዋል፤ በተጨማሪም በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመስራት በሚያስችላቸው አቅጣጫ ላይ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ከዶ/ር ንጉሥ ታደሰ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከአሁን ቀደም መጋቢት 6 እና 7 ቀን 2017 ዓ/ም በአካባቢው ካሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ መምህራን፣ የማስተማር እና ምዘና ዘዴዎች (Instructional and assessment methods)፣ የትምህርት አመራር እና አስተዳደር (Educational leadership and management) እና ቱቶሪያል ፕሮግራሞች (Tutorial programs) በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡