የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም የጥናት ውጤት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር ተካሄደ ፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) የወደፊት አቅጣጫ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም ጥናት ውጤት ለአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር መስከረም 14 ቀን 2018 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ ተካሄደ ፡፡
በመርሀ- ግብሩ ላይ የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ዶ/ ንጉሥ ታደሰ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የዕለቱ መርሀ-ግብር ተቀዳሚ ዓላማ በዋናነት በሚቀርበው የጥናት ውጤት እና በወደፊት የትግበራ ሂደት ላይም የጥናቱን ውጤት በአግባቡ ተረድቶ ለመተግበር እንዲቻል ግንዛቤን መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የዚህ ጥናት ዉጤት በዋናነት ባለፈዉ ለአካዳሚክ ሰራተኞች ይፋ እንደተደረገ አስታዉሰዉ ፣በዚህ መድረክ የአስተዳደር ሰራተኞች ጋርም በዉጤቱ ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖር መደረግ ስላለበት እና ሰራተኛዉም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ንጉሥ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ያለበትን ደረጃ በመገምገም እንደ አዲስ እንዲደራጅ መንግስት ያደረገው ልዩ ዉሳኔ ለዩኒቨርሲቲውና ለተቋሙ ማህበረሰብ ትልቅ ትንሰኤ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያለበትን ደረጃ በጥልቀት በመመልከት መልካም ተሞክሮዎችን የበለጠ ማስቀጠልና መሻሻል የሚገባቸውንም ለይቶ በማረም እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ሥም በማረም የህዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡ በመቀጠልም “አሁንም ተቋሙ በተለይ በተደራጀ መልክ ሲቀጥል አገልግሎታችንን ማዘመን ብቻ ሳይሆን ዘመኑ የሚፈልገዉ ሁነን መገኘት አለበን ፡፡ እይታችን አጭር መሆን የለበትም ፤ ሁሉም ሰራተኛ በእኔነት ስሜት ከሰራ የወደፊት ጉዞአችን እና ስራችን የልፋታችንን ዉጤት የሚከፍል ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ባለፈዉ በስራ መጀመሪያቸዉ በሰራተኛዉ የቀረቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለእያንዳንዱ የተቀመጡ አቅጣቻዎች እና የተወሰኑ ዉሳኔዎችን አቅረበዋል፡፡